=<({አል-ኢኽላስ 112:1-4})>=
ﺑﺴﻢ ﺍﻟﻠﻪ ﺍﻟﺮﺣﻤﻦ ﺍﻟﺮﺣﻴﻢ
1. በል! እርሱ አላህ አንድ ነው።
2. አላህ (የሁሉ) መጠጊያ ነው።
3. አልወለደም፤ አልተወለደምም።
4. ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም።
![]() =<({አል-ቁርአን 96:1-5})>=
![]() በቡኻሪ በተዘገበው ሐዲስ መሰረት እውቀትን መሻት በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው። ![]() |
---|
ሂጃብና ኒቃብ እንዲሁም ቡርቃ የብዙ አለመግባባትና የክርክር አርዕስቶች ከሆኑ ብዙ ዘመናትን አሳልፈዋል። ብዙ ሃገሮች እነዚህን ሃይማኖታዊ አልባሳት የከለከሉ ሲሆን አንዳንድ ሃገሮች ደግሞ የት የት ቦታ መለበስ እንዳለባቸው ገደብ አስቀምጠዋል።
በኒቃብ እና በቡርቃ ላይ ብዙ ክርክሮች የተደረጉ ሲሆን ኒቃብ ጭቆናና ኋላቀርነት ነው የሚሉ ትችቶችም ከተለያዩ ሰዎች ይሰነዘራል። እናም ዛሬ የምናየው እውነት ኒቃብ እና ቡርቃ የኋላቀርነት እና የጭቆና መገለጫዎች ናቸውን? የሚለውን ነው።
=<({አል-ቁርአን 33:59})>=
{59} አንተ ነብይ ሆይ! ለሚስቶችህ ፣ ለሴት ልጆችህና ለምእመናን ሚስቶችም መከናነቢያቸውን በሙሉ አካላቸው ላይ ይለቁ ዘንድ ንገራቸው። ይህ እንዲታወቁና (ነፃና የተከበሩ ስለመሆናቸውና) በባለጌዎች እንዳይደፈሩ ለመሆኑ በጣም የቀረበ ነው። አሏህም አዛኝ መሃሪ ነው።
እንደ አጠቃለይ በየትኛውም የአለም ክፍል የሚኖሩ ሙስሊም ሴቶች እራሳቸውን በሂጃብ ሲሸፋፍኑ፤ በተወሰኑ ሃገሮች የሚገኙ ሙስሊም ሴቶች ደግሞ እራሳቸውን በኒቃብ እና በቡርቃ ይሸፋፍናሉ።
ኒቃብና ቡርቃ ኢስላማዊ መሠረት ያላቸው ስለመሆኑ ምንም የሚያማያጠራጥር እና ጥያቄ የማያስነሳ ጉዳይ ነው። ቀደምት ሙስሊም ሴቶችም እራሳቸውን በነዚህ አልባሳት ይሸፋፍኑ እንደነበር ብዙ የታሪክ መዛግብት ያመላክታሉ።
ሆኖምግን ኒቃብና ቡርቃ ግዴታ ናቸው ወይንስ በፍላጐት የሚደረጉ ናቸው በሚለው ዙርያ ኡለማዎች ተለያይተዋል። ለዛምነው አንዳንድ ሙስሊም ሴቶች ሂጃብ ይለብሳሉ፤ ሌሎች ደግሞ ኒቃብን ወይም ቡርቃ የሚለብሱት።
ኒቃብ የሚለብሱ ሙስሊም ሴቶች ይህን የሚያደርጉት በራሳቸው ፋቃድና ውዴታ ሲሆን አንዱ የአምልኮት ተግባር እንደሆነ ፣ኢስላምን ነፃነት እና ከሃራም ነገር መጠበቂያም እንደሆነ በማመን ጭምር ነው። ትልቁ ጭቆና ግን ኒቃብ መልበስ ሳይሆን ሙስሊም ሴቶች ሃይማኖታቸውን እንዳይተገብሩ መከልከል ነው።
ውዷ እህቴ ሆይ! ሂጃብና ኒቃብ ጭቆና ነው የሚሉ ሰዎች ለአንች ተጨንቀው እንዳይመስልሽ የሚያጠቁበት፤ የእምነቱን ስርአት የሚያበላሹበትን መንገድ በአንች በኩል እየፈለጉ ቢሆን እንጅ። ውድ እህቴ ሆይ! ኒቃብ መልበስ ጭቆናነው ብለው የሚለፍፍ ሰዎች የሐራም ነገሮችን እና የዝሙት ባህርን ሊያስቀዝፉሽ መሆኑን እወቂ!!!
ኒቃብ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የፋሽን ልብሶች አካል አይደለም። ይልቁንም ጊዜና ቦታ የማይገድበው ሃይማኖታዊ ልብስና የአምልኮት ተግባር ነው። ይህ ደግሞ መቼም ቢሆን ጊዜ የማይሽረው ጉዳይ ነው።
ውዷ እህቴ ሰዎች ሂጃብ ፣ ጅልባብ ፣ ኒቃብ ፣ ቡርቃ መልበስ ኋላቀርነት ነው ስላሉሽ ዘመናዊ ሴት ለመባል ብለሽ ሂጃብሽን አታውልቂ። ሂጃብሽን እና ኒቃብሽን በማውለቅ የአሏህን ህግጋት ጥሰሽ እንዴት ለማይረባ የሰው ልጅ ትችት እጅ ትሰጫለሽ?
እራስሽንም ለስላሳ ሙስሊም ብለሽ አትጥሪ! ይህን በማለትሽ ብዙ ሃራም ነገሮችን እንድትሰሪ ትገፋፊያለሽና። ለዛም ነው ዛሬ ላይ የሂጃብንና የኒቃብን ትርጉም ሳይረዱ ፀጉራቸውን ብቻ ሸፍነው ሱሪ የሚለብሱ እንዲሁም ትንሽ ሰፋ ያለች ልብስ ካላቸው ያስጠብቧትና የአካል ቅርፃቸው እንዲታይላቸው የሚያደርጉ ሙስሊሞች እየተፈጠሩ ያሉት። ትዳር ፈልገሽ ከሆነ ቶሎ አግቢ እንጅ በዚህ ስም አምላክሽን አሏህ አታምፅ።
ሂጃብሽንም ሆነ ኒቃብሽን በትክክል በመልበስሽ ሙስሊሙ ኡማ ባንች ይኮራል። ላንችም ያለውን ውዴታና ፍቅር አትዘንጊ። ከዚህም በላይ አሏህ ላንች ያለውን ውዴታ አስታውሽ። ሂጃብሽንና ኒቃብሽን በትክክል በመልበስሽ የኢስላም አምባሳደር ስትሆኝ፤ የታላቅነትን ፣ የነፃነትን እና የንፁህነትን አክሊል ትጎናፀፊያለሽ።
ኒቃብና ቡርቃ መልበስ በምንም ተአምር የሴቶችን የበታችነት አያመላክትም። በራሳቸው ፍቃድ ከሚለብሱ ሙስሊሞች እውነታጋ ይቃረናል።
ኒቃብ የለበሰች ሴት ኒቃብ በመልበሷ ማህበራዊ ትስስር ከመፍጠርም ሆነ በማህበራዊ ጉዳዮች ዙርያ ከመሳተፍ የሚያግዳት ነገር አይኖርም። ያ ጉዳይ ሃራም እስካልሆነ ድረስ ማለት ነው። እንዲሁም ኒቃብ መልበስ ለኢኮኖሚ እድገት አስተዋፅኦ ከማድረግም ሆነ በከፍተኛ የትምህርት ተቇማት እውቀትን ከመሻት የሚያግዳት ነገር የለም።
ኒቃብ የሚለብሱ ሆነው በጣም የተማሩ፤ ስራቸውን በብቃት የሚሰሩ ሴቶች በርካታ ናቸው። እናታችን አኢሻ(ረ.ዐ) እንደ ምሳሌ ብናነሳ አኢሻ(ረ.ዐ) ኒቃብ(ብርቃ) የምትለብስ ታላቅ አሊም ነበረች። ሆኖምግን እውቅ የሆነች አሊም ከመሆንና ወንዶችንና ሴቶችን ሰብስባ ከማስተማር አላገዳትም ነበር።
የማህበረሰቡ ወግ ልማድ በአብዛሃኛው ሰው ተቀባይነት ያለው እስከሆነ ድረስ ምንም ነገር አይፃረርም። ኒቃብ ቅዱስነት እንጅ ወንጀል አይደለምና። የማህበረሰባችንን ባህል ወግ ልማድም የሚፃረረው እራስን በኒቃብ መሸፋፈን ሳይሆን ሃፍረተገላን መገላለጥ ነው።
ውድ እህቴ ሆይ! ከላይ የጠቀስኴቸው መሠረተቢስ ትችቶች ከሃዲዎችና ሙናፊቆች በሙስሊም ሴቶች ስም የራሳቸውን ፓለቲካዊ አጀንዳና በኢስላም ላይ ያላቸውን ጥላቻ የሚነዙባቸው የድንቁርና ሃሳቦች እንጅ ሌላ አይደሉም።
መነኩሴዎች ፣ የቡድሂስቶችና የሂንዱ እምነት ተከታዮች እራሳቸውን በመሸፋፈናቸው እንደ ቅዱስ ከመታየታቸው በላይ ይከበራሉ። ሙስሊሞች ሲሆኑ ግን እንደ አሸባሪና የደህንነት ስጋት ተደርገው ይቆጠራሉ። ለምን ይሆን?
ኒቃብ ጭቆና አይደለም የማህበረሰቡን ወግ ልማድ የሚፃረር የደህንነት ስጋትም አይደለም። ይልቁንም የሙስሊም ሴቶች ፍላጎት ከመሆኑ በላይ የበለጠ ወደ ጌታቸው የሚቃረቡበት ነው።
አንዲትን ሴት አስገድዶ ኒቃብ ማስለበስ ጭቆና እንደሆነው ሁሉ በፍላጎቷ ኒቃብ የለበሰችን ሴት አስገድዶ ማስወለቅ ጭቆና እና ግፍ አይደለምን?
ውድ እህቴ ሆይ! አሏህ መልካም ወደሆነ ነገር እንዲመራሽ የምትፈልጊ ከሆነ ሂጃብሽንና ኒቃብሽን አሏህ ባዘዘሽ መሠረት ልበሽ። ራስሽንም ለትዕዛዙ ተገዥ አድርጊ። ማማርሽም ሆነ ማጌጥሽ በሂጃብሽ ላይ ይሁን።
የወጣቱ ተልዕኮ አድራሻ
ኢስላማዊ መጽሐፎችን ያውርዱ |
---|